
ጸሐፊ፡ ኤደን ሲሳይ ስርጉ
“ባሕል ሰዎችን አይቀርጽም ፤ ሰዎችን ባሕልን ይቀርጻሉ።” ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቺ
እያንዳንዱ ትውልድ አነስተኛ የዕድገት ጭላንጭልን ይወርሳል፤ ነገር ግን ያንን ወደ ዘላቂ ለውጥ መቀየር የራሱ ኃላፊነት ነው ብዬ አምናለሁ። አያቴ ትምህርት የሰዎችን ህይወት መለወጥ እንደሚችል ታምን ነበር። በሷ ዘመን በሴቶች ላይ ተጥለው የነበሩት ገደቦች ከባድ የነበሩ ቢሆንም፣ እርሷ ግን በጽናት ታግላ የነርሲንግ ድግሪዋን ማግኘት ቻለች። በስራዋም እሷ ያላገኘቻቸውን እድሎች ለልጆቿ ፈጥራለች። አያቴ እናቴን ያሳደገቻት የሰው ልጅ አላማ በአገልግሎት መንፈስ መኖር እንደሆነ አስተምራ ነው፡፡ በአያቴና በእሷ ትውልድ መስዋዕትነት ምክንያት፣ እናቴ የሴቶችን መብት ይበለጠ በሚቀበል ዓለም ውስጥ የተሻለ ትምህርት ማግኘት ቻለች። በእናቴና በአያቴ ጥንካሬ ተከብቤ ሳድግ የኔ ዋጋ የሚለካው ማህበረሰቤን በምጠቅምበት መንገድ እንደሆነ ተማርኩ።
ሆኖም ግን እያደግኩ ስመጣ አያቴና እናቴ ያጋጠሟቸው ፈተናዎች እንዳልጠፉ፤ ሴቶች አሁንም በእኩልነት እንደማይታዩ ተመለከትኩ። ይልቁንም በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በጾታ እኩልነት ላይ እየጨመረ በመጣው ተቃውሞ ምክንያት መልካቸውን ቀይረው በአዲስ መልክ ጥቃቶች መተዋል። ትንኮሳን፣ የሴት ጥላቻን፣ ሆን ተብለው የሚሰራጩ የሐሰት መረጃዎችን እና የሐሰት ምስሎችን በመጠቀም፣ ስለ የሴቶች መብት የሚናገሩ ወጠቶችን ዝም ለማሰኘት የሚሰሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ተስፋፍተዋል። ዩኒቨርሲቲ በገባሁበት ወቅት የገጠሙኝ ፈተናዎች፣ በጾታ ላይ የተመሰረተ ጥቃት፣ ትንኮሳ እና ደካማ የተቋማት ጥበቃ ፣ የተለዩ ሳይሆኑ የብዙ የኢትዮጵያ ሴቶች የዕለት ተዕለት መደበኛ የሕይወት ገጠመኞች እንደ ነበሩ ተረዳው።እነዚህ ችግሮች ተስፋ የሚያስቆርጡ ቢሆኑም፣ ያደግኩበት ሁኔታ ግን እነዚህ ነገሮች ልክ እንዳልሆኑና እኔም አካባቢዬን ለመለወጥ አቅም ያለኝ ሰው እንደሆንኩ በማሳየት ተስፋ እንዳልቆርጥ ረዳኝ።አንድ ጓደኛዬ ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው የሎው ሙቭመንት ከተባለ ማህበር ጋር ስታስተዋውቀኝ ሃሳቤ ትክክል እንደነበረ አረጋገጥኩ፡፡
የሎው ሙቭመንት የዩኒቨርሲቲ ግቢዎችን ደህንነታቸው የተጠበቀ ለማድረግ እና በእህትማማችነት፤ በምክር እና በድጋፍ የሴት ተማሪዎችን አቅም ለማብቃት የሚሰራ የተማሪዎች ኅብረት ነው።በየሎው ሙቭመንት ውስጥ ባለኝ ተሳትፎ ወጣቶች በጋራ ለአንድ ዓላማ ሲሰሩ ያለውን ኃይል ተመለከትኩ። ። ወጣቶች ለውጥ ከተቋማት ብቻ እስኪመጣ መጠበቅ አያስፈልገንም። ይልቁንም ደህንነታቸው የተጠበቀ ስፍራዎችን በመፍጠር፣ ሴቶችን በመደገፍ እና በማህበረሰባችን ውስጥ ያሉ ጎጂ አመለካከቶችን በንቃት በመጋፈጥ ልዩነት ማምጣት ላይ ማተኮር እንችላለን።
ከሌሎች በወጣቶች ከሚመሩ ማህበራት ጋር አብሮ መስራት ይህንን እምነቴን ይበልጥ አጠናከረው። በገጠር አካባቢዎች በራሳቸው ትምህርት ቤቶችና ማህበረሰቦች ውስጥ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚሰሩ ወጣቶችን አገኘሁ። ወጣት ወንዶች ያደጉበትን አስተሳሰብ በመቀየር ለሴቶች መብት እንዲቆሙ የሚያበረታቱ ማህበራትን አየሁ። እንዲሁም በመላው አፍሪካ ወጣት ሴቶች በአመራር ቦታዎች ላይ እንዲካተቱ የሚሰራው ሺ ሊድስ ፕሮጀክት ከእኛ ጋር ባለው ትስስር፤ የእኛ ትግል የኢትዮጵያ ሴቶች ብቻ ሳይሆን የአህጉራችን ሴቶችም ትግል እንደሆነ ተረዳሁ። የብርታትም ምንጭ ሆነኝ።
ወጣቶች እነዚህን ጥረቶች ሲመሩ ማየቴ፣ ለውጥን ለመጠየቅ ብቻ ሳይሆን በገዛ ማህበረሰባቸው ውስጥ ለውጥን ለመፍጠርም ብቃት እንዳለን አሳየኝ። ከዚህም በተጨማሪ፣ ከእነዚህ የተለያዩ ንቅናቄዎች ጋር ያለኝ ግንኙነት የወጣቶች እንቅስቃሴ መቼም አንድ ዓይነት መሆን እንደማይቻል ተረድቻለሁ። በኢትዮጵያ ውስጥ የፆታ እኩልነት አስፈላጊ የሆነ መሰለታዊ ለውጥ የሚያመጣ ቢሆንም በየቦታው የሚመጣበት መንገድ ይለያያል፡፡ ከተማ ውስጥ ያሉ ሴት ተማሪዎች እና የገጠር ሴቶችንና ሴት ልጆችን የተለየ ተጨባጭ የኑሮ እውነታ በመገንዘብ አካሄዳችንን ማስተካከል ይገባናል፡፡ወጣቶች ባሉበት ሆነው ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ ማሳመን እና አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠት፣ ለውጡ ሁሉንም አካታች እንዲሆን ለማድረግ ዋናው መንገድ ነው። በየራሳችን ጥረቶች ዉስጥም ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ ፣ አካል ጉዳተኛ የሆኑ፣ እንዲሁም በተለያዩ የሃይማኖትና የኢኮኖሚ ደረጃዎች ላይ ያሉ ሴቶችን ማካተት አለብን፡፡ ውይይቶቻችንን ከማበልጸግ ባለፈ፣ አካታችነት በማኅበረሰቡ ዘንድ ብዙ የማይነሱ ጥያቄዎችን በማንሳት ትርጉም ያለው ውይይት እናመጣለን።
ይህ ግንዛቤዬ ህግ ለመማር ከወሰንኩባቸው ምክንያቶች ውስጥ ዋናው ነው ። በነጻ የህግ እርዳታ መስጫ ማዕከላት ውስጥ ከሚሰሩ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ጋር በምሠራበት ጊዜ ፤ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶችን በየቀኑ ለመርዳት ምን ያህል ቁርጠኝነት እንደሚያስፈልግ እናም እንደ ሀገር የሴቶችን መብት ለማስከበር ምን ያህል መሄድ እንደሚቀረን አይቻለሁ። በምሠራበት ወቅት ካየሁት የጥቃት ታሪኮች፣ ችግሩ የመነጨው ማኅበረሰባችን ለሴቶች ካለው ዝቅተኛ ዋጋና አመለካከት እንደሆነ ከዕለት ወደ ዕለት ይበልጥ ግልጽ እየሆነልኝ መጣ።የሕግ ማዕቀፎች ሊጠነክሩ የሚችሉት እነሱን በሚያስፈጽመው የማኅበረሰብ አስተሳሰብ ልክ ብቻ እንደሆነ ተገነዘብኩ። በወረቀት ላይ የሰፈሩት የሕግ ጥበቃዎች በሚተገበሩበት ጊዜ ጥቃት የደረሰባቸውን ወገኖች በጥልቀት በሰረፁ ባህላዊ አመለካከቶች ምክንያት የሚደረግላቸው አያያዝ ተጎጂዎች ይበልጥ እንዲጎዱ ያደርጋቸዋል።
አንዲት ሴት ጥቃት በሚደርስባት ጊዜ “እንዴት ይህ ሆነ?” ይባላል፤ ነገር ግን ከመሠረቱ “እንዴት ነው ጥቃት የሚመጣው?” የሚለውን ሐሳብ ለመፈተሽ ፈቃደኛ መሆን ያስፈልገናል።ለውጥ የሚመጣው እነዚህን ጥያቄዎች ስናነሳ፣ ስንመረምር እና ለመለወጥ አስበን ስንንቀሳቀስ ነው።ይህ ተሞክሮ የየሎው ሙቭመንት እና በወጣቶች ማህበራት ላይ ያለኝን ትልቅ ተስፋ አሳድጎታል። ወጣቶች ባሕልን ተቀብለን ማቆየት ብቻ ሳይሆን፣ ቀይረነው ለማስቀጠልም ኃይል አለን። በጋራ ያለንን ኃይል ወደ ጾታ እኩልነት ስናዞረው፣ ለቀጣይ ትውልዶች የተሻለ አመለካከት እናወርሳለን።በአሁኑ ጊዜ እንደ የሎው ሙቭመንት ያሉ የወጣቶች ማኅበራት የሚጋፈጡት ከኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን፣ ጥላቻን በመንዛትና ሴቶችን በማዋረድ የሚደሰቱ የኢንተርኔት ላይ ካሉ ቡድኖችም ጨምሮ ነው።
የኢትዮጵያ ወጣቶች ለማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦች መምጣት ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ማዕከላዊ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል። ለዚህም አንዱ ግልጽ ምሳሌ በ1960ዎቹ እና 1970ዎቹ የነበረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ነው፤ በወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ለውጥን ለማምጣት በተቃውሞ፣ ፖለቲካዊ ውይይቶችን እና ንቁ ተሳትፎዎችን ተጠቅመዋል። የእነሱ ንቅናቄ ወጣቶች የአገር አቀፍ ንግግሮችን የመቅረጽ እና ማህበረሰቡን ወደ ለውጥ የመግፋት ኃይል እንዳላቸው ያሳየል። ይህ በወጣቶች የሚመራ የለውጥ ሂደት በኢትዮጵያ ብቻ የተገደበ ሳይሆን በመላው የአፍሪካ አህጉር የሚታይ ሰፊ አዝማሚያ ነው። በአፍሪካ ታሪክ ውስጥ የወጣቶች ንቅናቄዎች የማህበረሰባቸውን የወደፊት እጣ ፈንታ እንደገና በመቅረጽ ረገድ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ለውጦችን ሲመሩ ቆይተዋል። ከቅኝ አገዛዝ ጋር በተደረገው ትግል ወቅት እንደ ጋና እና ደቡብ አፍሪካ ባሉ ሀገራት የተማሪዎች
ንቅናቄዎች ነጻነትን ለመጠየቅ ተንቀሳቅሰዋል፤ ይህም የወጣቶች ንቅናቄ ሴቶችን የሚነኩ ችግሮችን ጨምሮ እንዴት መታገል እንደሚችል አመላካች ነው።
የየሎው ሙቭመንት እና ሌሎች በመላ ሀገሪቱ በዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ውስጥ የሚገኙ ማህበራት፣ ይህንን መንፈስ በመውሰድ ወደ ጾታ እኩልነት ማዘዋወር እየሰሩ ይገኛሉ። በሁሉም የሕይወት ዘርፍ የወጣቶች ተሳትፎ ማበረታታት እጅግ አስፈላጊ ነው፤ምክንያቱም ወሳኝ ጥያቄዎችን ወደ ማኅበረሰቡ የውይይት መድረክ በማምጣት፣ ጠቃሚ የሆኑ ውይይቶች እንዲቀሰቀሱ የማድረግ ሀይል ይሰጠናል። በዚህ መንገድ ወጣቶች ፖሊሲዎችን የመቅረጽ እና መሪዎችን እርምጃ እንዲወስዱ የመጫን አቅም አለን፡፡ይህ ንቁ ተሳትፎ በተለይ የሕግ ማሻሻያዎችን ለማምጠት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡እንደ ዲጂታላዊ ጥቃቶችን የሚከላከሉ ተጨባጭ ማዕቀፎች ወይም በመሠረታዊ የስነ-ተዋልዶ ጤና ምርቶች ላይ የተጣለውን ታክስ የሚያስቀሩ ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎችን ለማምጣት የጎላ ሚና ሊኖረን ይገባል።
በነፃ የሕግ ምክር መስጫ ማዕከላት ስሰራ እና በወጣቶች ማኅበር ውስጥ አባል በመሆን ያገኘኋቸው ልምዶች የጾታ እኩልነትን ለማምጣት በየደረጃው እርምጃ መውሰድ እንደሚያስፈልግ ያለኝን እምነት አጠናክረውታል። ሴቶችን በቀጥታ የሚደግፉ ተሟጋቾች እንደሚያስፈልጉት ሁሉ፣ ጎጂ ስርአቶች በሌሎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ከመቀጠላቸው በፊት የሚያስቆሙ ወጣቶችም ያስፈልጋሉ። ከአንድ ትውልድ ወደ ቀጣዩ እንደሚተላለፍ ሻማ ሁሉ፣ ማህበራዊ እድገትም ሊቀጥል የሚችለው ወጣቶች ነበልባሉን ለመጠበቅና ወደ ፊት ለማራመድ ሲመርጡ ብቻ ነው።
በኢትዮጵያ ለሴቶች መብት እና ለፆታ እኩልነት የሚደረገው ትግል ከብዙ ዘመናት ጀምሮ በበርካታ ሴቶች የተቀረፀ ነው።ይሁን እንጂ ዕድገት ዘላቂ አይደለም፤ እንደ ወጣት ሴቶች ያለፉት ትግሎች ያስገኙት መብቶች ተጠቃሚዎች ብቻ ሳንሆን ጠባቂዎችም ነን። ለሴቶች መብት ስንሰራ የሚሰነዘር ተቃውሞ ቢኖርም በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ሴቶችና ልጃገረዶች እነዚህን መብቶችና ዕድሎች በእኩልነት እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ አለብን። እኔ ያለሁት በእናቴና በአያቴ መስዋዕትነት ላይ ነው። የእነርሱ ትግል እኔ አሁን የምጓዝበትን መንገድ አብርቶልኛል። እናም እንደ ወጥት ፣ የእኔ ኃላፊነት እነርሱ በብዙ ድካም ያስገኙልኝን መብቶችና ዕድሎች ከእኔ በኋላ ለሚመጡ ወጣት ሴቶችም ማዳረስ ነው።
Telegram | LinkedIn | Instagram | TikTok | Twitter/X | Facebook

